“ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” የአካባቢ ብክለት መከላከል ከተማ አቀፍ ንቅናቄ በድሬዳዋ ተጀመረ
ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም
ድሬዳዋ
===============
“ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ሦስተኛው ዙር የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ በተገኙበት በይፋ ተጀመሯል።
በንቅናቄው መድረኩ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከዲር ጁሀር፣ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የጸጥታ አካላት፣ ተማሪዎችና መምህራን ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች በመድረኩ ተገኝተዋሉ።
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከዲር ጁሀር ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት ለመከላከል “ፅዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ በሀገር አቀፍና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ደረጃ በመከናወኑ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት የሚካሄደው ሦስተኛው ዙር “ፅዱ ኢትዮጵያን፣ ፅዱ ድሬዳዋን ለትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ ለቀጣይ ሦስት ወራት የሚከናወን ሲሆን፣ በቀደሙት ዙሮች የተመዘገቡ ውጤቶችን ማጠናከርና ወደ ቀጣይ ደረጃ ማሸጋገር ዋና ዓላማው መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል።
በቀደሙት ዓመታት በ“ፅዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ በድሬዳዋ ከ5,000 በላይ ሰዎች በአካል ግንዛቤ የተፈጠረላቸው ሲሆን፣ ከ400,000 በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች መረጃ ተደራሽ በማድረግ ግንዛቤና ተሳትፎአቸውን ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመት ለሦስት ወራት በሚካሄደው ንቅናቄ በዋናነት በሦስት ዘርፎች ላይ ትኩረት ይደረጋል። እነሱም፦ የፕላስቲክ ብክለት፣ የአደገኛ ቆሻሻና ኬሚካሎች አያያዝና አወጋገድ፣ እንዲሁም የድምፅ ብክለት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ በመግለጽ በእነዚህ ዘርፎች ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የአካባቢ ሕግን ማስከበርና ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ይጠብናል ብለዋል።
ከንቲባ ከዲር ጁሀር አክለውም የፕላስቲክ ቆሻሻ በአካባቢና በሥነ-ምህዳር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በ2017 ዓ.ም የጸደቀውና በጥር 2018 ዓ.ም ወደ ትግበራ የገባውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ መሠረት በማድረግ የፕላስቲክ ከረጢቶችን አጠቃቀም ለመቆጣጠር የሕግ ማስከበር ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
“ይህ ሥራ በአንድ ተቋም አቅም ብቻ የሚሳካ አይደለም” ያሉት ከንቲባው፣ በተለይም የጸጥታ አካላትና ሌሎች ተዛማጅ ተቋማት በቅንጅትና በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ መመሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎችም የፕላስቲክ ከረጢቶችን በመተው አማራጭ የአጠቃቀም ዘዴዎችን በመምረጥ አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ጊዜያቸው ያለፈ ኬሚካሎችን በመለየት በአግባቡ ማስወገድ፣ ለማስወገድ የማይገባቸውን በጥንቃቄ ማከማቸት፣ ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎችን መለየትና ተገቢውን የመልሶ ጥቅም ሂደት ማስፈጸም፣ እንዲሁም በጤና ተቋማት የሚመነጩ አደገኛ ቆሻሻዎችን አያያዝና አወጋገድ ማሻሻል ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ሕይወት መመናመንና የአካባቢ ብክለት ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚሹ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በቀደሙት ሁለት ዙሮች የተገኙ ውጤቶችንና መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናቀርና በማስፋፋት፣ ለሀገራችን ዘላቂ ልማት፣ ለዜጎች ጤናማና ንጹሕ አካባቢ እንዲፈጠር እና ለመጪው ትውልድ ፅዱ ኢትዮጵያን ለማስረከብ በጋራና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣዮቹ ሦስት ወራትም በፕላስቲክ፣ በአደገኛ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎች እንዲሁም በድምፅ ብክለት ላይ በተቀናጀ መልኩ ለመሥራት ሁሉም ተዛማጅ አካላት በቅንጅት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም የሦስተኛው ዙር “ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” ንቅናቄ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ አስፈላጊውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።