"ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ" ንቅናቄ አካል የሆነ የውይይት መድረክ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠየቀ ።
ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም
፡፡፡፡፡፡፡፡፡።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
"ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ" ንቅናቄን እውን በማድረግ ለትውልዱ ለማስተላለፍ መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ተደራሽነትና የግንዛቤ ፈጠራ ሚናቸውን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ጠየቁ ።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጋር በመተባበር ሁለተኛው ዙር “የጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ላይ ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች እና ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታው ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራርና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፥ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ ከምትሰራቸው የልማት ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን አንስተዋል።
የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ፕላስቲክን በአካባቢ ተስማሚ ምርቶች ለመተካት የተጀመረው ስራም እንደ ሀገር አዲስ ልምድ እና የሚደነቅ ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል።
ለተግባራዊነቱና ለስኬቱም መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ግንዛቤ የሚፈጥሩ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።
አካባቢን መጠበቅ ጤናን መጠበቅ በመሆኑን ጤናችን ከተጠበቀ ሌሎችን የልማት ስራ መስራት እንደሚቻል በመግለጽ በብክለት ሳቢያ የሚደርሱ የጤና እክሎችን ቀድሞ በመከላከል የበለጸገችና ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የአካባቢ ጥበቃ አምባሳደር መሆን እንዳለበት ጠይቋል ።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ እንዳሉት፥ መንግስት ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሰፋፊ የልማት ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት፣ህጎችን የማሻሻል፣ አረንጓዴ አሻራና የወንዝ ዳርቻ የልማት እና ጽዱ ኢትዮጵያ ስራዎች በስፋት መሰራታቸውን አብራርተዋል።
አዲሱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ በብክለት ምክንያት በአካባቢና በሰዎች ደህንነትና ጤና ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ለአካባቢ ብክለት የሚዳርጉ እና አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ስስ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም ላይ ክልክላ በማድረግ በሥርዓተ ምህዳር ላይ የሚያደርሱትን ጉዳትን መቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል ።
አምራቾች ከማምረት ባሻገር ብክለትን በመከላከል ረገድ የራሳቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ በማድረግ በኩል እድል የሚሰጥ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፥ የሚዲያ አካላት የህዝብን አመለካካት ለመቀየር ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ለማድረግ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
====================================
የኢፌዲሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን
ቀጣዮችን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን ቤተሰብ ይሁኑ