የተቀናጀ የአካባቢ ሕግ ተከባሪነትን በማረጋገጥ በአካባቢ እና ማኅበረሰብ ላይ ሊደርስ የሚችልን ብክለት መቀነስ እንደተቻለ ተመላከተ
ታኅሣሥ 16 2018 ዐ.ም
አዳማ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
በአምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ ብክለትን ለመቀነስ ጥብቅ ክትትል እና ድጋፍ በመደረጉ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተገለፀ።
ይህ የተገለፀው ዛሬ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከፌዴራል፣ከክልሎች እና ከከተማ መስተዳደሮች ለተወጣጡ የዘርፍ መሥሪያ ቤት የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ቁጥጥር እና ክትትል ኃላፊዎች በተዘጋጀው የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና ላይ ነው።
ከየክልሉ ለተወጣጡ ኀላፊዎች የተዘጋጀው ሥልጠና ዋነኛ አላማው ሕጎችን፣ አዋጆችን፣እንዲሁም ደንብና መመሪያዎችን ጠንቅቆ በማወቅ የአካባቢ ሕግ ተከባሪነትን ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ለማስቻል መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሪክተር ክብርት ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት ተናግረዋል።
እንደ ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ገለፃ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የአካባቢ ሕግ ተከባሪነትን ለማረጋገጥ የብክለት ቅነሳ ስልቶችን በመቀየስ ተከታታይነት ያለው እና ሁሉን አካታች የሆነ ብሔራዊ የብክለት ቅነሳ ስራዎች መሠራታቸውን ገልፀው አበረታች ውጤት እየተመዘገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ም/ዋና ዳይሪክተሯ አክለውም በክቡር ጠ/ሚኒሥትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ጠንሳሽነት እየተካሔደ የሚገኘውን የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በተሳካ ሁኔታ ግብ እንዲመታ ተቋማቸው ያላሰለሰ ጥረቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሰልጣኞች በበኩላቸው አደገኛ ኬሚካል አያያዝና አጠቃቀም ወቅት ሊደርሡ ሥለሚችሉ ችግሮች፣ የማዕድን ምርት ለማምረት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወቅት የአካባቢ ህግጋትን ስለማክበር፣ እና የአካባቢ ፍቃድ አሰጣጥን አስመልክቶ ለጠየቁት ጥያቄዎች የተቋሙ ምክትል ዋ/ዳይሪክተር ማብራሪያ እና ገለፃ አድርገዋል።
ለአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ቁጥጥር እና ክትትል ኃላፊዎች የተዘጋጀው ስልጠና በቀጣይ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አስተዳደር አዋጅን፣የአካባቢ እና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማን፣የማምረቻ ተቋማት የአካባቢ አረንጓዴ ሰርተፊኬት ምንነትን እና ሌሎች ህግ ነክ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በሚሰጥ ስልጠና እንደሚቀጥል ከፕሮግራም መምሪያው መረዳት ይቻላል።
====================================