የሁለተኛው ዙር “ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ” የአካባቢ ብክለት መከላከል የክልል አቀፍ ንቅናቄ ፕሮግራም በማዕድንና በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው አሶሳ ከተማ ተካሄደ፡፡
ሁለተኛው ዙር
የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ የትግበራ መድረክ መርሃ-ግብር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት “ፅዱ ኢትዮጲያን ባህል ማድረግ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም የክልሉ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ፤ የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የዞን፣ የከተሞችና የወረዳዎች አመራሮች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች እና የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በድምቀት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን የንቅናቄው ማስጀመሪያ መድረኩ ላይ በመገኘት በከፈቱበት ወቅት ከለውጡ ወዲህ የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ ጽዱ ኢትዮጵያን ማረጋገጥ የብልጽግና አንዱ ተግባር ነው ብለዋል። አያይዘውም ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ በሚል የተጀመረው ሃሳብ ለሀገራችን ብልጽግና መረጋገጥ አዎንታዊ ሚና ያለው፤ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት መፈፀም የሚገባው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት አንስተው ሁሉም አመራርና ፈጻሚ በንቃት እንዲሳተፍ የስራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ክብርት ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአመራሮቿ ቁርጠኛ አስተባባሪነት እና በውድ ልጆቿ ተሳትፎ በአንድ ጀንበር ከ700 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በተግባር ያሳየችበት ቀን ማግስት በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ ንቅናቄ የትግራ ሂደት መጀመሩ ለየት ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የሁለተኛው ዙር ንቅናቄ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ በማጎልበት በስድስት አበይት ጉዳዮች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም አካባቢዎች የሚካሄድ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በንቅናቄ ወራቶች ውስጥ ከ15 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ህዝብ የገፅ-ለገፅ ግንዘቤ እንዲሁም ከ50 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍል በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ መረጃ ተደራሽ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የአንድ ተቋም ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካላትና የዜጎችም ሁሉ ሀላፊነት በመሆኑ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ፅዱ፣ ንጹህና ጤናማ አካባቢ ለትውልድ ለማስተላላፍ መንግስትና ሁሉም ህዝብ የጎላ ሚና እንዳላቸዉና ለዚህም በተለይም አካባቢ ጥበቃን በሚመለከት የወጡ የአካባቢ ህጎችን መፈጸምና ማስፈጸም፣ ስለአካባቢ ብክለት አሳሳቢነት ህብረሰተቡን ማስገንዘብ፣ አካባቢን የሚበክሉ አካላትን በጋራ ተጠያቂ ማድረግ፣ አካባቢ የመጠበቅና መንከባከብ፣ የአካባቢ ተቆርቋርቋሪና አምባሳደር መሆን እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
የሁለተኛው ዙር ክልል አቀፍ የአካባቢ ብክለት መግቻ ንቅናቄ የመወያያ ጽሁፉ ቀርቦ ሰፊ ውይይት በማድረግ ገለጻ ተደርጎል፡፡ የሁለተኛው ዙር ንቅናቄ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ የከተማ ጽዳት ዘመቻ፣ በፓናል ውይይት እንዲሁም በአሶሳ ከተማ እየተገነባ ያለውን የከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ግንባታን በመስክ ጉብኝት በማድረግ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል፡፡
====================================
የኢፌዲሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን
ቀጣዮችን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን ቤተሰብ ይሁኑ