ብሔራዊ የባዮሴኩዩሪቲ ማዕቀፍ ትግበራ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ ወርክሾፕ ተካሄደ ።
መስከረም 26/2018 ዓ.ም
@*
የደህንነት ህይወትና ወራሪ መጤ ዝርያዎች ተግባራትን ለመደገፍ የሚያስችል ብሔራዊ የባዮሴኩዩሪቲ ማዕቀፍ ትግበራ ፕሮጀክት ተጀመረ ።
ፕሮግራሙን በንግግር ያስጀመሩት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ዘመናዊ ባዮቴክኖሎጂ የግብርና ምርቶችን በማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እንዲሁም የሰዎች ጤናን ለማስጠበቅ የሚያስችል ጠቃሚ ቴክኖሎጂ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህን ዘመናዊ ባዮቴክኖሎጂ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለመጠቀም ከልውጥ ህያዋን ዝውውር ጋር በተያያዘ የሚነሱ የደህንነት ጉዳዮች፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በበቂ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው ይገባል ብለዋል ፡፡ ይህንንም መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ የልውጥ ህያዋን ድንበር ዘለል ዝውውርን ለመቆጣጠር የተደነገገውን የካርታኄና ፕሮቶኮል አባልና ፈራሚ ሀገር ስትሆን ባለሥልጣን መስሪያ ቤታችንም የዓለም አቀፍ ስምምነቱን አተገባበር እንዲከታተል በአዋጅ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ፕሮቶኮሉን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች ማለትም የደህንነተ-ህይወት (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 896/2007፣ የተለያዩ ማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያዎች ፀድቀው ስራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል ፡፡
እንዲሁም ከወራሪ መጤ ዝርያዎች ጋር በተያያዘ በሀገራችን ከ 35 በላይ የመጤ ወራሪ ዝርያዎች እንደሚገኙ በጥናት መለየታቸውን፤ ከእነዚህም የመጤ ወራሪ ዝርያዎች መካከል እንቦጭ፣ የወያኔ ዛፍ፣ ነጭ ለባሽ፣ የወፍ ቆሎ፣ አቀንጭራ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸው በማብራራት የወራሪ መጤ ዝርያዎች ሥርጭት በኢትዮጵያ በስርዓተ-ምህዳር፣ በብዝሃህይወት፣ በአካባቢ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የሚያደርሱት ተጽዕኖ ቀላል የማይባል መሆኑን ተናግረዋል ። ይህንንም ለመቆጣጠር የወራሪ መጤ ዝርያን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል ፡፡
እየታዩ የሚገኙትን ክፍተቶች ከግምት በማስገባት የልውጥ ህያው ዝርያዎች ዝውውር በህገወጥ መንገድ እንዳይከናወን እንዲሁም የወራሪ መጤ ዝርያዎች መስፋፋትንና ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፌደራል እስከ ክልል ብሎም ወረዳ ባሉ መዋቅሮች የተለያዩ ስልቶችና የአሰራር ስርዓቶችን ለመዘርጋትና ለማጠናከር፣ የአቅም ግንባታን ለማሳደግ እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን አጠናክሮ ለመተግበር የሚያስችል ብሔራዊ የባዮሴኩሪቲ ማዕቀፍ (national biosecurity framework) ማዘጋጀት እና ተግባራዊ ማድረግ ማስፈለጉን ገልጸዋል ።
ክብርት ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ አክለውም ከዚህ በፊትም የባዮሴፍቲ ፕሮጀክት ተቀርጾ ሲተገበር መቆያቱን እና መሰረታዊ ለውጥም መምጣቱን አንስተው ይህ ፕሮጀክትም ሳይንሳዊ እውቀትና ልምድን በመጠቀም የወራሪ መጤ እና ልውጥ ህያው ዝርያዎች ዝውውር ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመለየትና መፈተሽ፣ ለመከታተልና ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር የሚያስችል ብሔራዊ የባዮሴኩሪቲ ማዕቀፍ በመገንባት ተቋማዊ አሰራሮችን ማጠናከርና ከሌሎች ተቋማትጋር በተጣጣመ መልኩ በማከናወን የዝርያዎችን ተጽእኖ ለመቀነስ ዓለማ ያለው መሆኑን አብራርተዋል ፡፡