የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጀዋር፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ፣ ከፍተኛ የከተማ አመራሮች ፣ እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በድሬዳዋ በፓናል ውይይት እና በከተማ የኮርደር ልማት እንዲሁም የመኪና ጭስ በ80% የሚቀንስ የቴክኖሎጂ የማስተዋወቅ ዙሪያ የተሰሩ ሥረዎችን በመጎብኘት በከፍተኛ ድምቀት በይፋ ተጀምሯል።
የአከባቢ ብክለቶችን በዘላቂነት ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራሮችና የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው የጠቀሱት ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጀዋር ቆሻሻን በመፀየፍና አወጋገዳችንን በማዘመን መልሶ በመጠቀም የገቢ ምንጭ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀጣይ የአከባቢን ብክለት ለመከላከል በተቀመጡ አቅጣጫዎች ህብረተሰቡን በዘመቻ በማሳተፍ ፣ የዕምነትና የትምህርት ተቋማትን ፣ የአገልግሎት ሰጭዎችንና ፋብሪካዎችን ሞዴል ሆነው የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአከባቢ ብክለት እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት ለመከላከል በተለያዩ ጊዜ የወጡ ህጎች በአግባቡ እንዲፈፀሙ የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ፅዱ ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ስራ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ በንቅናቄ እንደሚሰራ ተናግረው፤ የሱፐር ቴክ ቴክኖሎጂ ድሬዳዋ ላይ ስራ መጀመሩ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለውም ገልፀዋል።
የኢፌደሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው የፕላስቲክ አወጋገዶችን በአግባቡ በማስወገድ የአየር ብክለትን መከላከል እንደሚገባ በመግለጽ ለሚመጣው ትውልድ ከአባቶቻችን የተረከብናትን ጽዱና ንፁህ ኢትዮጵያን ለማስረከብ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
የድሬዳዋ አከባቢ ጥበቃ ም/ዋና ዳይሬክተርም የቆሻሻ አወጋገዳችንን በማዘመንና የአከባቢ ጥበቃ ስራዎችን በትኩረት በመስራት ጽዱ ኢትዮጵያን ለትውልዱ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአከባቢ ብክለትን ለመከላከልና እያስከተለ የሚገኘውን ጉዳት በዘላቂነት ለማስቆም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራዎቻችንን ማጠናከር ፣ ደኖችን መንከባከብና ተራራዎችን ማልማት ፣ የወጡ አዋጆችን ማስፈፀም ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ፣ የድምጽ ብክለቶች ማስወገድ ፣ የቆሻሻ አወጋገዶችን ማዘመን ፣ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀምና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ ለዜጎች ለኑሮ ንፁህና ምቹ አከባቢ መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።