የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ አለማችንን ከሚያሰጓት ትልልቅ ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑ ተገለፀ።
ህዳር 11/2018ዓ.ም
=============
አለም አቀፍ የጸረ -ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል። የጸረ-ተህዋስያን መድሐኒቶች በጀርሞች መለመድ በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ጤና እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ያለ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ሲሆን ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጤና ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት በጸረ- ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ምክንያት በዓለም ላይ ከ1.27 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በየአመቱ እንደሚሞቱ ተገልጿል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ በግንዛቤ ማስጨበጫ መክፈቻ መድረኩ ላይ እንደገለፁት አግባብ ያልሆነ የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች አጠቃቀም መድኃኒቶች በበሽታ አምጪ ተህዋስያን በቀላሉ እንዲለመዱ በማድረግ በሰው፣ በእንስሳትና አካባቢ ጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር በመገንዘብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለቀጣይ አምስት አመታት የሚቆይ ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን ይፋ አድርገዋል። ሚኒስትሯ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የጸረ -ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ''አሁን እንተግብር፦ዛሬን እንጠብቅ፣የወደፊታችንን እናረጋግጥ'' በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ እንደሚገኝ ገልፀው ችግሩን ለመቀነስ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣የሚዲያ አካላት፣የእንስሳትና የአካባቢ ጤና ባለሙያዎች፣ የጤና ቁጥጥር አካላት፣ፓሊሲ አውጪዎች ብሎም የመላው ማህበረሰቡ ተሳትፎን የሚጠይቅ መሆኑ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ኢ/ር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በሰው ፣ በእንስሳትና በአካባቢ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር በመገንዘብ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እያካሄደ ባለው የፅዱ ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ጋር በማቀናጀት እየሰራበት እንደሚገኝ በመጠቆም ተግባሩን በማጠናከር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራት እንዳለበት በመጠቆም ፅዱ ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ራዕይ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር እና ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የቀጣዩን አምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ትግበራ ለማሳካት የጋራ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋሉ።