የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሠራተኞች እና የበላይ አመራሮች የሴቶች ቀንን /march 8/ በተለያዩ ሁነቶች አከበሩ።
መጋቢት 18/ 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
የዕለቱ መርሃ ግብር "50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለዕኩልነት እና ለበለፀገች ኢትዮጽያ" በሚል መሪ ሃሳብ የተቋሙ ሠራተኞች እና የበላይ አመራሮች በተገኙበት በተለተያዩ ሁነቶች ተከብረዋል ።
የአመራርነት ክህሎት ከሚዳብርባቸው መንገዶች አንዱ መልካም ተሞክሮን መቅሰም እንደሆነ በማመን የተቋሙ ም/ዋና ዳይሪክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ የህይወት እና የአመራርነት ልምዳቸው ቀርቧል።
በክብርት ዋና ዳይሪክተር ዶ/ር ለሊሴ ነሜ አቅራቢነት በተካሔደው የሕይወት ልምድ ተሞክሮ በአስተዳደግ፣ በትምህርት፣ በፖለቲካ ተሳትፎ እና በአመራርነት ዘውግ ዘርዘር ያሉ አስተማሪ እና አዝናኝ ገጠመኞች ቀርበው መማማሪያ ሆነዋል።
ክብርት ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው ሕይወት የትግል፣የፅናት እና የመስዕዋት ውጤት መሆኗን በማውሳት ሠራተኞች በተለይም ሴቶች ያለባቸውንን ድርብርብ ችግሮች በመታገል ለውጤት እንዲተጉ አሳስበዋል።
የሴቶች ቀንን ለመዘከር ዛሬ እየተከበረ በሚገኘው በዓል የሴቶችን የአመራርነት ሚና ማላቅ ለሀገር ብልፅግና ምን አሥተዋፅኦ እንዳለው በዝርዝር ቀርቧል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አበባ መጫ የሴቶችን መብት እና እና ዕኩልነት የሚዳስስ የሃምሳ ዓመት ታሪክ አቅርበው ውይይት ተካሒዶበታል። በውይይቱ በሴቶች ላይ ሲደርሱ የነበሩ ማህበራዊና መዋቅራዊ ጫናዎች በዝርዝር ተብራርቷል።
እንደ ወይዘሮ አበባ ገለፃ የሴቶችን ተሳትፎ ማበረታታት እንደተቋምም እንዲሁም እንደሀገር ለምናልመው ለውጥ ሁነኛ መሰረት ይሆናል ብለዋል።
በዕለቱ መርሃ ግብር በአዋጅ ቁጥር 1383/2017 ክልከላ የተጣለበት የፕላስቲክ ከረጢትን አስመልክቶ ትምህርታዊ ጭውውት ቀርቧል። የዛሬው መርሃ ግብር ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ለማብቃት፣ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል በመግባት ተቋጭቷል።