የብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታን በላቀ አፈፃፀም ለመተግበር እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ
መጋቢት 9 2018ዓ.ም
አዲሥ አበባ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አካባቢያዊ ብክለት እና ብክነትን በመቀነስ የተሳካ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት አቅዳ ፖሊሲዎችን፣ ህጎችን፣አዋጆችን በማዘጋጀት እና በመተግበር እንዲሁም የተለያዩ ዓለማቀፍ ሥምምነቶችን በመፈረም በርካታ ሥራዎችን አያከናወነች ትገኛለች።
በ2017 ዓ.ም የፅዱ ኢትዮጽያን እሳቤ በማሳካት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የታመነበት የብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ፀድቆ ወደ ትግበራ ገብቷል።
ከፍኖተ ካርታው ዓላማዎች መካከል አንዱ ከልማዳዊው መንገድ "Take make dipose" አምርት- ተጠቀም - ጣል ሥርዓት በመውጣት የሃብት አጠቃቀም ሥርዓትን በተቻለ መጠን በዘላቂነት ለመጠቀም ወደ መልሶ መጠቀም ሥርዓት እንዲሸጋገር ማስቻል ነው። ይህ ፅንሰ-ሃሳብ በአካባቢ ሃብቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቀነሥ ለዘላቂ የአካባቢ ሃብት አጠቃቀም መርሕ ጉልህ አስተዎፅኦ ያበረክታል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ አተገባበር የታለመለትን ግብ እንዲመታ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር በሕብረት ለመስራት የሚያስችል የጋራ ሥምምነት ውል አስሯል።
በተካሔደው የፍርማ ሥነስርዓት የኢትዮጽያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የኢንዱሥትሪ ሚኒስቴር፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት፣ የፊንላንድ ኤምባሲ እንዲሁም የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ዶ/ር ለሊሴ ነሜ የብሔራዊ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ ተቋማት በስራ ዕቅዳቸው፣ በአሰራር ሥርአታቸው እንዲሁም በሥራ አተገባበራቸው ወቅት አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
ክብርት ዶ/ር ለሊሴ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ሥርዓት ተጠናክሮ ውጤት እንዲያመጣ ሥምምነቱን የፈፀሙ አካላት በአራት አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ አብራርተዋል። በማብራሪያቸው መሠረትም የፖሊሲ እና የቁጥጥር ማዕቀፍ፣ መሠረተልማት እና ፈጠራ፣ አቅም ግንባታ እንዲሁም ድጋፍ እና ክትትል ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።
ከተለያዩ የዘርፍ መስሪያ ቤት በፍርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ የተሳተፋ ከፍተኛ ኅላፊዎች በበኩላቸው ሥምምነቱ ፍሬ እንዲኖረው በየበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።